የምግብ ዋስትናን ያረጋገጡ ሴት አርሶአደሮች

/አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/

ሴት አርሶአደሮች የቤት እመቤትነትን አጥር አፈራርሰው  በግልም ሆነ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የግብርና ስራዎች ላይ በመሰማራት ራሳቸውን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ከማላቀቅ አልፈው ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ጉልህ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ሴት አርሶአደሮች በርካታ ናቸው፡፡ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በርካቶች ተሸልመዋል፡፡ በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ዞን በወንዶገነት  ወረዳ የወተት ላሞች እርባታ ባለቤት ወ/ሮ አሰለፈች አሰፋ፣ የተቀናጀ  ግብርናን በትክክል እየተገበሩ ያሉ  ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ወርቁ እና  በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን በምዕራብ አበያ ወረዳ  ፍቅር የሐር ትል ጥጥ ፍተላ ማህበር አባላት ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

ወ/ሮ አሰለፈች አሰፋ በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ዞን  በወንዶገነት ወረዳ  የወተራና ቀጨማ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ዘመናዊ የወተት ላሞች  እርባታ አላቸው፡፡ ወ/ሮ አሰለፈች እንደነገሩን የዛሬ 20 ዓመት የነበራቸው አንድ የሀገር ውስጥ ዝሪያ ላም  በቀን ትሰጥ የነበረው ወተት  ሁለት ሊትር እንኳን ስለማይሞላ  የገቢ ምንጫቸው መሆኑ ይቅርና ለቤተሰብ ፍጆታም የማይበቃ ነበር፡፡ ያላቸው የእርሻ መሬትም በጣም አነስተኛ ስለሆነ ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነበር፡፡ አንድ ቀን ሻሸመኔ ዘመዶቻቸው ጋር ሲሄዱ የተሻሻሉ  የፈረንጅ ላሞችን  ያያሉ፤ የሚሰጡትን የወተት ምርታቸውንም ይሰማሉ፡፡ በዚህም ተገፋፍተው  ከባለቤታቸው ጋር በመመካከር  1 የተጠቃች ምርጥ ዝሪያ ጊደር በ1,300 ብር ገዙ፡፡ እርባታውንም ጀመሩ፡፡

ወ/ሮ አሰለፈች ከ12 ዓመት በፊት ባለቤታቸው ድንገት  በሞት ሲለያቸው በሃዘን ቢጎዱም ልጆቻቸውንም ሰብስበው በመያዝ ዘመናዊ የወተት ላሞች እርባታን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ በርትተው ሰሩ፤ ድህነትንም ረቱ፡፡  ዛሬ 9 ላሞች፣ 3 ጊደሮች እና 7 ጥጆች በአጠቃላይ 19 ከብቶች  አላቸው፡፡ አንድ ላም በቀን ሁለት ጊዜ የሚትታለብ ሲሆን ከአንድ ላም  በአንድ ጊዜ አለባ እስከ 10 ሊትር ወተት ያገኛሉ፡፡ አሁን  ከሚታለቡት ላሞች በአንድ ቀን የሚገኘውን የወተት ምርት ለቤተሰብ ፍጆታ የሚበቃቸውን አስቀርተው በአንድ ቀን 60 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ አንዱን ሊትር በ60 ብር ይሸጣሉ፡፡ በአንድ ቀንም 3,600 ብር ገቢ ያገኛሉ፡፡

ወ/ሮ አሰለፈች ብቻቸውን በዚህ ስራ ልጆቻቸውን አሳድገው በደንብ አስተምሯቸዋል፡፡ ሁለቱ ዲግሪያቸውን ይዘው የመንግስት ስራ ይሰራሉ፡፡ የመጨረሻዎቹ ሁለት ልጆቻቸው ደግሞ 12ኛ ክፍል አጠናቅቀው ከእሳቸው ጋር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

 

“አሁን ለመንቀሳቀሻ የሚሆነኝ ጥሬ ገንዘብ 2 ሚሊየን ብር ያለኝ ሲሆን  ወደፊት በቂ የማርቢያ ቦታ ወስጄ የያዝኩትን ዘመናዊ የወተት ለሞች እርባታን ይበልጥ ለማስፋት እቅድ አለኝ፡፡” ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ዓለማፀሐይ ወርቁ  በወንዶ ገነት ወረዳ የአበዬ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ አግብተው የቤት እመቤት ሆነው ከልጆቻቸው ጋር ቤት ይዉሉ ነበር፡፡ የቀበሌያቸውን አርሶአደሮች የሚትደግፈውን የግብርና ባለሙያ ትምህርትና ምክርን ተንተርሰው በ2005 ዓ.ም በ10 የእንቁላል ዶሮዎች እርባታውን ጀመሩ፡፡ የተቀናጀ ግብርናን በመተግበር ውጤታማ ሆነዋል፡፡ የዶሮ እርባታን፣ የኩሬ ዓሳ እርባታን፣ የከብት እርባታን፣ የንብ እርባታን እና የሐር ትል እርባታን በአግባቡ ተግብረዋል፡፡ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬን በጓሮ ያለማሉ፡፡ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን አረጋግጠው በክልልና በፌዴራል ደረጃ ተሸልመዋል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ የግብርና ምርቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብ በማቅረብ የስርዓተ-ምግብ ችግሮችን መቅረፍ ላይ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ዛሬ በአንድ ዙር 3,000 የአንድ ቀን ጫጩቶችን አሳድገው አንዱን በ170 ብር ይሸጣሉ፡፡ ከሚያረቡት  ከ50 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች በአንድ ቀን 40 እንቁላል ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ አንድ ምርጥ ዝሪያ የወተት ላም በ28,000 ብር ገዝተው አርባታ የጀመሩ ሲሆን አሁን 5 የሚታለቡ የወተት ላሞች፣ 2 ጊደሮች፣ 4 ጥጆች በጠቅላላ 11 ከብቶች አላቸወ፡፡ በአንድ ቀን 80 ሊትር የወተት ምርት ለገበያ በማቅረብ አንዱን ሊትር በ60 ብር ሂሳብ ሽጠው በቀን 4,800 ብር ገቢ ያገኛሉ፡፡ ከኩሬ ዓሳ እርባታም በዓመት ሁለት ጊዜ አምርተው ለገበያ ያቀርባሉ፡፡

ስልጠና ወስጄ የሐር ትል ልማትን በ2016 ዓ.ም እኔ ነኝ በአካባቢው የጀመርኩት ያሉት አለምፀሐይ፣ በዓመት አራት ጊዜ ቢያመርቱም አንድ ኪሎ የሐር ጥጥ የሚሸጥበት 220 ብር በቂ ስላልሆነ ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግ እሰት ጨምሮ መሸጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ንብ እርባታም በ2 ቀፎዎች በ2015 ዓ.ም በመጀመር ዛሬ 27 ቀፎዎች እንዳላቸው የጠቀሱት ወ/ሮ ዓለምፀሐይ ግማሾቹ አዲስ የገቡ ስለሆኑ በ2016 ዓ.ም ወደ 20 ኪሎ ግራም ማር አምርተው ለገበያ ማቅረባቸውን ገልፀዋል፡፡

በውጤታማነታቸው በ2014 ዓ.ም እንደ ሲዳማ ክልል የምግብ ዋስትናን ካረጋገጡ ሴት አርሶአደሮች ተመርጠው ከፌዴራል ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡ ዘንድሮም እንደ ክልል ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ ዛሬ ቋሚ ንብረታቸውን ሳይጨምር ያፈሩት ሀብት ወደ 8 ሚሊዮን ብር ይገመታል፡፡

እስከ አሁን ለ5 ሰራተኞች የስራ እድል የፈጠሩት ወ/ሮ ዓለምፀሐይ፣ ወደፊት እነዚህን ስራዎች ይበልጥ አስፋፍቼ ለሌሎችም የስራ ዕድል በመፍጠር በአርአያነት ለመቀጠል አቅጃለሁ ብለዋል፡፡

ሌሎች ውጤታማ የሆኑት ሴት አርሶአደሮች ፍቅር  የሐር ትል ጥጥ ፍተላ ማህበር አባላት ናቸው፡፡ በደቡብ ኢትዮየጵያ ክልል ጋሞ ዞን በምዕራብ አበያ ወረዳ የኡጋዮ ቀበሌ ነዋሪዎች ናቸው፡፡  አሁን ያሉት የማህበሩ አባላት 15 ሲሆኑ ራሳቸው የሐር ኩፕኩፓ (የሐር ጥጥ) ያመርታሉ፤ በኡጋዮ ቀበሌ ውስጥ የሐር ኩፕኩፓ የሚያመርቱ 446 ሴቶች ስላሉ ከነሱም የሚፈልጉትን ያህል ይገዛሉ፡፡  ወደ ሐር ክር በመቀየር እሰት ጨምረው ለገበያ ስለሚያቀርቡ ጥሩ ገቢ ያገኛሉ፡፡

የፍቅር የሐር ጥጥ ፍተላ ማህበር ሰብሳቢ ወ/ሮ ሙሉነሽ ኤና እንደገለፁት በፊት በባል ስር ሆነው በኢኮኖሚ ጥገኝነት ይኖሩ ነበር፡፡ እግራቸውንና እጃቸውን አጣጥፈው የባለቤታቸውን እጅ ይጠብቁ ነበር፡፡ ከወረዳው ግብርና ባለሙያዎች ባገኙት  ግንዛቤ መጀመሪያ  በ51 ሴቶች ነበር  በ2008 ዓ.ም ‘ፍቅር የሐር ትል ጥጥ አምራቾች ማህበር’ በሚል ስም የተደራጁት፡፡ በዛን ጊዜ የሚያመርቱትን የሐር ኩፕኩፓ 1 ኪሎ በ30 ብር ይሸጣሉ፡፡ ገበያዉም ቀዝቃዛ ስለበር የማህበሩ አባላት እየለቀቁ አሁን ያሉት አባላት ብቻ ቀሩ፡፡  የቀሩት 15 አባላት ሥራቸውን አጥብቀው እየሰሩ ስልጠና ወስደው በድጋፍ ባገኙት የመደወሪያ መሽኖች በ2011 ዓ.ም ወደ ፍተላ ስራ ገቡ፤ እሰት ጨምረው መሸጥ ጀመሩ፡፡ ዛሬ የኢኮኖሚ ነፃነታቸውን አውጀው በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ በማህበር የቆጠቡትን ብር ዓመት ሲሞላ  የተወሰነውን ብር በማስቀረት ሌላውን ይከፋፈላሉ፡፡ በክፍፍል ጊዜ ሁሉም እንደየስራቸው እስከ 30 ሺህ ብር የሚያገኙ አሉ፡፡ አሁን ከማህበሩ አካውንት ወደ 30 ሺህ ብር አላቸው፡፡

አንዷ  አባል የሰራችውን ነው የሚታገኘው፡፡ በሳምንት አንድ ኪሎ ግራም የሐር ጥጥ ክር ካመረተች በ2,000 ብር ሽጣ 400 ብር በጋራ ቁጠባ ከቆጠበች 1,600 ብር ትወስዳለች፤ ለቤተሰብ ፍጆታ የሚያስፈልገውን ተጠቅማ የቀረውን በግሏ ትቆጥባለች፡፡ የማህበሩ አባላት የሰሩትን ያህል ስለሚያገኙ በከፍተኛ ተነሳሽነትና በውድድር መንፈስ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለላቀ ውጤትም በተነሳሽነትና በውድድር መንፈስ መስራትን አጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡  


Please publish modules in offcanvas position.

We use cookies to improve your experience on our website. By browsing this website, you agree to our use of cookies.