በልማት የበረቱ ድህነትን ረቱ!

/አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/

ሴቶች ግንባር ቀደም በመሆን የልማት ጀግንነታቸውን እያስመሰከሩ ይገኛሉ፡፡ በርትተው በመስራት የሀብት አቅም ፈጥረው ድህነትን የረቱ፣ ከራሳቸው አልፈው  ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት የራሳቸውን አስተዋፅዖ እያበረከቱ ያሉ ሴቶች በርካታ ናቸው፡፡ ከነሱ መካከል እርሱ ቢፈቅድ አነስተኛ የጫጩት ማሳደጊያ ማህበር እና ነፃነትና ቤተሰቧ የደሮ እርባታ ማህበር አባላትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ወ/ት ገነት ግዛው በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ዞን በወንዶገነት ወረዳ  የወሻና ሶየማ ቀበሌ ነዋሪ ናት፡፡ ወ/ት ገነት በ12+3  ትምህርቷን ጨርሳ  የመንግስት ሰራተኛ ነበረች፡፡ ወር ጠብቃ የሚታገኘው ደሞዝ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ከመግፋት በስተቀር ኑሯን እንደማይቀይር ከመረዳቷ ባሻገር ሌላ ቦታ በዚህ ስራ ውጤታማ የሆኑ ሰዎችን ማየት የአንድ ቀን ጫጩት የማሳደግ ስራን  እንዲትጀምር መነሻ ሆኗታል፡፡  ከሁለት እህቶቿ ጋር ተደራጅተው እርሱ ቢፈቅድ አነስተኛ የጫጩት ማሳደጊያ ማህበርን በ2012 ዓ.ም  በመመስረት  የማህበሩ ሰብሳቢ ሆነች፡፡

ስራውን  30 ሺህ ብር ከመንግስት ተበድረው የቀረውን ከቤተሰብና ከሌሎችም በመበደር ነበር የጀመሩት፡፡ ሲጀምሩ አንዱን ጫጩት በ42 ብር ሂሳብ ከኢትዮ ቺክን 2,000 ጫጩቶችን በመግዛት ነበር፡፡ በመጀመሪያው ዙር አሳድገው በ45 ቀናቸው  አንዱን በ60 ብር ሂሳብ ነበር የሸጡት፡፡ አሁን አንዱን ጫጩት በ146 ብር ገዝተው አሳድገው አንዱን በ170 ብር ሂሳብ ለመንግስትም ሆነ ለአርቢዎች ያቀርባሉ፡፡

እንደ ወ/ት ገነት ገለፃ በአንድ ጊዜ 2,000 ጫጩቶችን የሚያስገቡ ሲሆን በአመት  እስከ 4 ዙር አሳድገው ይሸጣሉ፡፡ ለሁለት ሺህ ጫጩቶች ብቻ የሚበቃ ማሳደጊያ ቤት በቤተሰቦቻቸው ግቢ ውስጥ ሰርተው ስለጀመሩ እስካሁን እሱን ነው የሚጠቀሙት፡፡ በግቢው ውስጥ በቦታ ጥበት ምክንያት ለማስፋፋት ባይመችም እሱን በጥንቃቄና በንፅህና በመያዝ ውጤታማ ሆነዋል፤ ለውጥም አምጠተዋል፡፡ ብድሩን በጊዜ መልሰው በራሳቸው ካፒታል ስለሚንቀሳቀሱ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያሉት፡፡ ኑሯቸውን በመለወጥ የእድገት ጎዳና ላይ ስለሆኑ ለአካባቢው ሴቶችም አርአያ ሆነው መልካም ተሞክሯቸው እንዲስፋፋ በር ከፍተዋል፡፡

“ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ተደርጎልናል፡፡ የጫጩት ማሳደጊያ ቤት ሲሰራ ፊድ ዘ ፍዩቸር (Feed the Future) በግንባታ እቃዎች ደግፎናል፡፡ በኔዘርላንድስ መንግስት በጀት የሚደገፍ ድርጅት (SNV) የኛን ውጤታማነት አይቶ ሶላር አስግብቶልን ብዙ ችግሮችን ፈቶልናል፡፡ በፊት መብራት ሲጠፋ ጫጩቶች ለብርድ ስለሚጋለጡና በጨለማ ስለማይበሉ የመሞት እድላቸው ከፍተኛ ነበር፡፡ እንዳይሞቱ ከሰል አቀጣጥለን አጠገባቸው እያደርን፣ እንዳይጨልምባቸው ደግሞ ጄኔሬተር እንጠቀም ነበር፡፡ አሁን ሶላሩ ከመብራት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሁሉ ፈቶልናል፤ የኛንም ድካም አቃሎልናል፡፡ ለጄኔሬተርና ለነዳጅ የምናወጣውን ወጪም ቀንሶልናል፡፡  እንዳሁም የሶላርና የዋናው መብራት ሲስተም ስለተገናኘ በክረምትና በዳመና ጊዜ የሶላሩ ሀይል ስለሚቀንስ ከዋናው መብራት ቻርጅ እያደረገ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ሶላሩ የጫጩቶችን ሞት ስለቀነሰልን በአጠቃላይ ለውጤታማነታችን ጉልህ አስተዋፅዖ አበርክቶልናል፡፡” ብላለች፣ ወ/ት ገነት፡፡

ከግብርና ባለሙያዎችም ሙያዊ ድጋፍና ምክር እንደሚያገኙ የጠቀሰችው ወ/ት ገነት፣ የማህበሩ አባላት  ያካበቱትን እውቀት በመጠቀምም በየቀኑ ጫጩቶቹን ራሳቸው እንደሚከትቡ ተናግራለች፡፡

ወደፊት የዶሮ እርባታውን ለማስፋፋት ቦታ ጠይቀዋል፡፡ ቦታ ሲያገኙ የአንድ ቀን ጫጩት ከማሳደግ ጎን ለጎን የእንቁላል ዶሮ እርባታና የስጋ ዶሮ እርባታ ለማካሄድ እንዲሁም በወረዳ ደረጃ የምርት መሰብሰቢያና ማከፋፈያ ማዕከል ለመገንባት አቅደው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ነፃነትና ቤተሰቧ የደሮ እርባታ ማህበር ሌላው ውጤታማ የሆነ ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ በሲዳማ ክልል ማከላዊ ዞን ይርጋለም ከተማ አስተዳደር በአቦስቶ 02 ቀበሌ ነው የሚገኘው፡፡ ማህበሩ በ200 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ደረጃውን የጠበቀ ቤት በመገንባት የእንቁላል ዶሮ እርባታ ከጀመረ 4 ዓመት ሆኗል፡፡ ማህበሩ በ2,500 ዶሮዎች የጀመረ ሲሆን እስከ አሁን  በ3 ዙር ዶሮዎችን አስገብቷል፡፡ አሁን ካሉት 2,500 ዶሮዎች በአንድ ቀን ከ1,700 በላይ እንቁላል ያመርታል፤ አንዱን እንቁላል እስከ 10 ብር በመሸጥ ጥሩ ገቢ እያገኘ ነው፡፡ ማህበሩ ወደፊት ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል የዶሮ እርባታውን የማስፋት ዕቅድ አለው፡፡

ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ሴቶች ውጤታማ እየሆኑ ናቸው፡፡ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትም የራሳቸውን አስተዋፅዖ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በአጠቃላይ የሴቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የእነዚህ ማህበራት ተሞክሮዎች ወደ ሁሉም አካባቢዎች መስፋፋት አለባቸው፡፡


Please publish modules in offcanvas position.

We use cookies to improve your experience on our website. By browsing this website, you agree to our use of cookies.