የምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት አበረታች ነው።የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ

(አዲስ አበባ፣ ግንቦት 24 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር የተቀናጀ የኢንስፔክሽን ቡድን በክልሎች የዘንድሮውን ዓመት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ሁኔታን ለመቃኘት በተደረገው የመስክ ምልከታ ግብረ-መልስ ላይ ውይይት ተካሄዷል።

የኢንስፔክሽን ቡድኑ ዋና ዓላማ የ2016/17 ምርት ዘመን የግብዓት አቅርቦት እና ስርጭትን ነባራዊ ሁኔታ መገምገም እና ክፍትቶችን ለይቶ እንዲስተካከሉ ማድረግ፣ የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ማድረግ፣ በአርሶ አደሩ የሚነሱ ቅሬታዎች በሚፈቱበት አግባብ ላይ በጋራ በመነጋገር የአቅርቦትና ስርጭት ስራውን የተሳለጠ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከመሰረታዊ የህብረት ሥራ ማኀበራት ጀምሮ እስከ ዩንየን ያለውን ክፍተቶች በመለየት እና የማስተካከያ ግብረ-መልስ በመስጠት በግብርናው ዘርፍ ትልቅ ዕምርታ ማምጣት ነው፡፡

በምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ እንደተናገሩት ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የተዋቀረ 6 የኢንስፔክሽን ብድን በ7 ክልሎች ላይ ከግንቦት 15 እስከ 21/2016 ዓ.ም ድረስ የምስክ ምልከታ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

የዘንድሮው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ቀድሞ መገዛቱና ወደ ሃገር ውስጥ በማጓጓዝ ወደ ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ማህበራት መሰራጨቱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑ ተናግረው የምርት ዘመኑ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት አበረታች ነው ብለዋል። በዚህም ምክንያት መንግስት በሰራው የተጠናከረ ስራ ህገ-ወጥ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውር ላይ ትልቅ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

 የግብርና ሚንስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በባለፈው የምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን በመረዳትና ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት በዘንድሮው የምርት ዘመን የተሻለ ስራ መስራት እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሣ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ እንደተናገሩት ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት አኳያ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የአፈር ማዳበሪያ ጭነው የገቡ የጭነት ተሽከርካሪዎች በአፋጣኝ ጭነታቸውን አራግፈው በመመለስ ቀሪ የአፈር ማዳበሪያውን ከወደብ ወደ ሃገር ውስጥ የማስገባት ስራ እንዲሰሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በውይይቱም ላይ ሁሉም የኢንስፔክሽን ቡድን በክልሎች ላይ ያደረጉትን የመስክ ምልከታ ሪፖርት በማቅረብ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭት ላይ የተሰሩ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር የታዩ ክፍተቶችን በማስተካከል በወቅቱ ለአርሶና ከፊል አርብቶአደሩ የአፈር ማዳበሪያውን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

የካሜራ ባለሙያ፡- ዮዲት እንዳለው

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው

 

 


Please publish modules in offcanvas position.

We use cookies to improve your experience on our website. By browsing this website, you agree to our use of cookies.