FDRE Ministry of Agriculture

የግብርና ኢንቨስትመንት ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የላቀ ድርሻ አለው፡፡

(አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

የግብርና ኢንቨስትመንትና ምርት ግብይት መሪ ስራ አስፈፃሚ ደረጀ አበበ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰፋፊ እርሻ የተሰማሩ 6 ሺህ  ባለሃብቶች መኖራቸውን ጠቅሰው እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ 4.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለግብርና ኢንቨስትመንት ለማስተላለፍ ውጥን ተይዞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለው በሆርቲካልቸር፣ በእንስሳት እና በሰፋፊ እርሻ እየለማ ያለው የአዝርት ልማት ላይ መሆኑንም መሪ ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡ በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ለማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻል፣ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዐድል ፈጠራ እና ለአግሮ ኢንዱስትሪው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆኑን አቶ ደረጀ ገልፀዋል፡፡

እንዲሁም ባለሃብቶች የእርሻ ስራቸውን በሚሰሩበት አካባቢ መንገድ ጥገና፣ ት/ቤት ግንባታ፣ ክሊኒክ ማቋቋም እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተቋማትን በመስራት  የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በማህበር እንዲደራጁ ግብርና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ስራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡

በየክልሉ ያሉ ባለሃብቶች ያሉበትን ቁመና በመፈተሽ እንደ አስፈላጊነቱ የአቅም ግንባታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተነግረው ለአብነትም የኢንቨስትመንት መሬት አለያይ፣ ክትትልና ድጋፍ አሰራር እንዲሁም የባለሃብት መረጃ አያያዝን ማዘመን ጉዳዮች ላይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን አቶ ደረጀ አብራርተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ባሌ ዞን በ2016/17 ምርት ዘመን በአርሶ አደሩ በአጠቃላይ በስንዴ የተሸፈነው 388 ሺህ 234 ሄ/ር መሬት ሲሆን በዚህም 13 ሚሊየን 588 ሺህ 190 ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡ በኢንቨስትመንት ደግሞ 10 ሺህ ሄ/ር መሬት በስንዴ የለማ ሲሆን በዚህም 500 መቶ ሺህ ኩንታል ምርት ይጠበቃል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ባሌ ዞን በግብርና ኢንቨስትመንት በተለይም በስንዴ ልማት የተሰማሩ ማህበራት ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

ቡላላ ዲንኪቲ እርሻ ንግድና ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ባሌ ዞን የሚገኝ በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማራ ማህበር ነው፡፡ የማህበሩ ስራ አስኪያጅ መኮንን ፀጋዬ ማህበሩ አራት የእርሻ ጣቢያዎች እንዳሉት ገልፀው ባልቻ የተባለ የስንዴ ምርጥ ዘር እያለማ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በቋሚነት 270፣ በጊዜያዊነት ደግሞ ወደ 250 ሰራተኞች እንዳሉት ስራ አስኪያጁ አብራርተዋል፡፡ በ2015/16 የምርት ዘመን 250 ሄ/ር መሬት በስንዴ እንደለማ ያስታወሱት አቶ መኮንን በዚህም 10 ሺህ ኩንታል መገኘቱን ገልፀዋል፡፡

በዘንድሮ የምርት ዘመን ከ 1 ሄክታር መሬት በአማካኝ 45 ኩንታል ምርት እና በአጠቃላይ ከማህበሩ ጣቢያዎች 28 ሺህ 500 ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቡላላ ዲንኪቲ እርሻ ንግድና ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግ/ማህበር በመንገድ፣ በት/ቤት እና በሆስፒታል ግንባታ ላይ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ ይገኛል፡፡

ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ

ፎቶግራፍ፡- ማቲዎስ ተገኝ

—————-

ስለግብርና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት፦

ድረ-ገጽ፦ www.moa.gov.et

ፌስቡክ፦ https://www.facebook.com/MoAEthiopia

ዩቲዩብ፦ https://www.youtube.com/@AgricultureEthiopia

ቴሌግራም፦ https://t.me/MoAEthiopianews

ቲዊተር፦ https://x.com/MoA_Ethiopia

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *