FDRE Ministry of Agriculture

የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ላይ የተሰራው ሥራ በሥርጭት ላይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ላይ የተሰራው ሥራ በሥርጭት ላይ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

(አዲስ አበባ፤ ግንቦት 7/2016 ዓ.ም፤ ግብርና ሚኒስቴር)

የግብርና ሚኒስቴር የአፈር ማዳበሪያ ግዥ እንዲፈፀም በሠራው ልክ ሥርጭቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የግብርና ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።

በሪፖርቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 16 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጅቡቲ መድረሱን፤ ከዚህም ውስጥ 11 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ከጅቡቲ ወደ አገር ውስጥ መጓጓዙን ተገልጿል።

በመስኖ ስንዴ ልማት በምርት ዘመኑ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 2 ነጥብ 97 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑም ነው በሪፖርቱ የተመላከተው።

50 ሚሊየን የአንድ ቀን ጫጩት ለማሠራጨት ታቅዶ 57 ሚሊየን ማሠራጨት መቻሉንና የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ለዚህ አስተዋፅዖ ማድረጉ ተገልጿል።

በ2016/17 በአረንጓዴ አሻራ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑና እስካሁን ባለው 6 ነጥብ 34 ቢሊየን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

ቋሚ ኮሚቴው በ2015/16 ምርት ዘመን በአፈር ማዳበሪያ የነበረውን ችግር በመፍታት በዘንድሮ ምርት ዘመን የግዥ ሥርዓቱን በማስተካከል ቀድሞ የማዳበሪያ ግዥ መፈፀም መቻሉ የሚበረታታ መሆኑን አስታውቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ሰለሞን ላሌ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት በርካታ ውጤታማና ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን አከናውነዋል ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የመስኖ ስንዴ ልማት ሥራውን በየዓመቱ በእጥፍ እያሳደገ መምጣቱ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን አመላካች መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአረንጓዴ አሻራና በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብሮችም አበረታች ውጤት መምጣቱንና አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበት ገልፀዋል።

የመስኖ ስንዴ ልማት ላይ አበረታች ውጤት መመዝገቡን አንስተው፤ የቡና ምርትን ለማሳደግም በዚሁ ልክ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

አሲዳማ መሬቶችን ለማከም ሚኒስቴሩ እያከናወነ ያለውን ሥራ ክልሎች እንዲደግፉት በማድረግ መሥራት እንደሚገባም ነው የገለጹት።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) በተያዘው የምርት ዘመን 16 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ መግባቱንና አምና በዚህ ወቅት የገባው 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ኩንታል እንደነበር አንስተዋል።

እስካሁን ባለው 11 ነጥብ 7 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደ አገር ውስጥ መጓጓዙን አንስተው፤ ከዚህም ውስጥ እስከ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው 6 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል መሠራጨቱን ገልፀዋል። ሥርጭቱንም ይበልጥ ለማቀላጠፍ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባከናወናቸው ተግባራት በተለይ አትክልትና ፍራፍሬዎች ላይ የዋጋ ለውጦች እንዲኖሩ ማስቻሉን ጠቁመዋል።

በዶሮና እንቁላል ዋጋ ላይም ቅናሽ መታየቱን ጠቅሰው፤ በስንዴና የሌማት ትሩፋት ላይ ያሉ ተሞክሮዎችን በማስፋት የቡናና ሌሎች ሰብሎች ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቦታል።