FDRE Ministry of Agriculture

በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙት የአሰሳና የርጭት አውሮፕላኖች ስራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ተካሄደ

(አዲስ አበባ፣ ሰኔ 08 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ተመስገን ጥሩነህ በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙ አምስት ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች /ኤር ትራክተርስ/ በይፋ ስራ አስጀምረዋል።

በይፋዊ የሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የናሽናል ኤር ዌይስ አመራሮች ተገኝተዋል።

ግብርናን ለማዘመንና መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ግብርና በእውቀት እና ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል። በዚህም ዘርፉን ለማዘመንና ለምርታማነት እድገት ወሳኝ ሚና ያላቸው በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙት 5 ዘመናዊ የአሰሳና የርጭት አዉሮፕላኖች ባለቤት መሆኗን የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ግርማ አመንቴ ዶ/ር ገልጸዋል።

ሚንስትሩ አክለውም አውሮፕላኖቹ ከግብርና ስራ በተጨማሪ ሌላ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ሲሆን ይህም የገቢ ምንጭ በመሆን ሌሎች ኤርክራፍቶችን ለመግዛት አቅም እንደሚፈጥሩ አብራርተዋል።

በ25 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቀው በቅረብ ጊዜ በ8 ክልሎች ተከስቶ የነበረው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ለመከላከል የአውሮፕላንና የሄሊኮፕተር ኪራይ ጨምሮ 13 ቢሊዮን ብር ከመንግስት ወጪ መዉጣቱን አስታውሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የአደጋ መቆጣጠሪያ የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች እንዲኖራት ትልቅ አገዛ አድርገዋል።

የናሽናል ኤር ዌይስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ ለሚ በበኩላቸው አገር በቀሉ ናሽናል ኤር ዌይስ አውሮፕላኖችን የማስተዳደርና የመቆጣጠር አገልግሎት ላለፉት 16 አመታት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው በተመሳሳይ ግብርና ሚኒስትር የገዛቸውን የርጭት አውሮፕላኖች አገልግሎት በመስጠት ለአንድ ዓላማ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም አውሮፕላኖቹን መጠቀም የሚያስችሉ ስምምነቶች ላይ የጋራ የፊርማ ስነ-ስርዓት ተካሂዶ መርሃ-ግብሩ ተጠናቋል።

ካሜራ፦ ዮዲት እንዳለው

ሪፖርተር፦ ጌዲዮን ነጋሽ