FDRE Ministry of Agriculture

መንግስት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ጉልህ ሚና አለው፡፡

/አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/

አምስተኛው የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የ2016 በጀት ዓመት ሁለተኛው ዙር የመንግስት እና ለጋሽ ድርጅቶች የጋራ የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ የፌደራል እና የክልል አመራሮች እንዲሁም የለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት እየተካሄደ ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) መንግስት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት፤ ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሚንስትር ዴኤታው አክለውም የመድረኩ አላማ መንግስት እና ለጋሽ ድርጅቶች የፕሮግራሙን የዘጠኝ ወር ዕቅድ አፈፃፀም በመገምገም በፌደራልና በክልል ደረጃ ሊፈቱ የሚችሉ ክፍተቶችን በመለየት ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ተወካይ ቤትሪስ ኔሪ በበኩላቸው አምስተኛው ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የተፈጥሮ አደጋ፣ የፀጥታ አለመረጋጋት እና የገንዘብ እጥረት ተግዳሮቶች እንዳጋጠሙት ተናግረዋል፡፡

ተወካይዋ አያይዘውም በፕሮግራሙ በተለያዩ መስክ የተሰማሩ አካላት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ሳይበግራቸው አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻላቸውን ጠቅሰው የበኩላቸውን ድርሻ የተወጡ አካላትን አመስግነዋል፡፡

የፌደራል እና የክልል ተቋማት የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች እየቀረቡ ሰፊ ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን የግምገማ መድረኩ ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡

የካሜራ ባለሙያ፡- ማቲዎስ ተገኝ

ዘጋቢ፡- ዮሐንስ ደመቀ