ለ2017/18 ምርት ዘመን ለአፈር ማዳበሪያ ግዥ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል- ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር)
(አዲስ አበባ፣ ጥር 30 ቀን 20 17 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
የአርሶ አደሩን የአፈር ማዳበሪያ ፈላጎት ለማሟላት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መንግስት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) የ2017/18 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ጋር በተያያዘ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሚኒስትር ድኤታዋ በዘንድሮ የምርት ዘመን 24 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ለመግዛት እቅድ እንደተያዘና ባለፈው ዓመት ከነበረው የ4 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ 13.5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ እንደተፈጸመ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት 6.4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተጓጉዞ ጂቡቲ ወደብ የደረሰ ሲሆን 4 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በባቡርና በጭነት መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ እንደገባም ተናግረዋል፡፡
ከባለፈው የምርት ዘመን የተረፈ ማዳበሪያ 3.1 ሚሊዮን ኩንታል ጋር በድምሩ ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ እንደሚገኝ በጋዜጣዊ መግለጫው ተመላክቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየቀኑም እስከ 100 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ በአሁኑ ሰዓት ወደ ሀገር ውስጥ እየተጓጓዘ እንደሆነም ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በዘንድሮ ዓመት 1.3 ቢሊዮን ዶላር ለማዳበሪያ ግዥ በጀት የተመደበ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት እና በሸማቹ ላይ ዋጋ እንዳይጨምር በማሰብ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በአንድ ኩንታል 3 ሺህ 700 ብር ድጎማ እንደተደረገ ሶፍያ ካሳ (ዶ/ር) አንስተው መንግስት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ከመቼው ጊዜ በተሻለ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪያው ለመስኖ፣ ለበልግ አብቃይ አካባቢዎች እንዲሁም ለመኸር የዘር ወቅት እንደሚውል የጠቅሱት ሚኒስትር ድኤታዋ ከፍተኛ ወጭ የወጣበት የአፈር ማዳበሪያው በአግባቡ አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስ ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ካሳሁን ማለቶ