(አዲስ አበባ፣ የካቲት 18 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በጃፓን መንግስት ድጋፍ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል፣ በግጭት ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎችን ለማገዝ እንዲሁም የግብርናውን ዘርፍ ለማጠከር 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር የሚተገበር ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
በአማራ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች ለአራት ዓመታት የሚተገበረውን የፕሮጀክት ድጋፍ ስምምነት የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ኃላፊ ኬንሱኬ ኦሺማ እና የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙድዚ ተፈራርመዋል።
ይህንንም ፕሮጀክት ለማስፈጸም የጃፓን መንግስት በጃይካ በኩል ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት እና ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ይሰራል።
የአርሶአደሩን ኑሮ ለማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል ያለመው ፕሮጀክቱ ከ27 ሺህ በላይ አነስተኛ አርሶአደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን 242 ሺህ ዜጎች የእውቀት ሽግግርና የአቅም ግንባታም ይፈጥራል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደተናገሩት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመከላከል መንግስት አበክሮ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
በጃፓን መንግስት ድጋፍ የሚተገበረውን ፕሮጀክት መሬት ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ከጃይካ እና ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ጋር በትብብር እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እንዳሉት የጃፓን መንግስት ላለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ይፋዊ የልማት ትብብር ሲያደርግ የቆየ መሆኑን ጠቅሰው ድጋፉ ለአቅም ግንባታ ኢንቨስትመንት፣ ለአነስተኛ ገበሬዎች ራስን ማስቻያነት እና ገበያ ተኮር ግብርና ልማት እንዲሁም የሩዝ ልማት ላይ የሚያተኩር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ፋራይ ዚሙዚዲ በበኩላቸው ለድጋፉ የጃፓን መንግስትን እና ጃይካን አመስግነው በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በአየር ንብረት ለውጥና በግጭት ምክኒያት የተጎዱ ማህበረሰቦችን መልሶ ለማቋቋም ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፍ፡- ማቲዮስ ተገኝ