FDRE Ministry of Agriculture

የተፋሰስ ልማት በአማራ ክልል

(አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

አማራ ክልል የዓባይ፣ የአዋሽ፣ የተከዜ እና የደናኪል ተፋሰሶች መገኛ ነው። ከአጠቃላይ የዓባይ ተፋሰስ ደግሞ 60 በመቶ የሚኾነውን የሚሸፍነው የአማራ ክልል ነው።

እንደ አሚኮ ዘገባ፤ ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም፣ አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሙሉ በሙሉ ወደ ዓባይ የሚፈስሱ ውኃማ አካላትን የያዙ አካባቢዎች ሲኾኑ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በከፊል የዓባይ ተፋሰስ ቀጣናዎች ናቸው።

የክልሉን የአፈር ክለት ለመከላከል እና በተፋሰሶች ሥር የሚገኙ ውኃማ አካላትን ከደለል ለመታደግ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት እና ጥበቃ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዳይሬክተር እስመለዓለም ምህረት ነግረውናል።

የጣና ሐይቅ እና የሕዳሴው ግድብ መጋቢ የኾነው የዓባይ ተፋሰስ ደግሞ አንዱ ትኩረት የተደረገበት ነበር። የዓባይ ተፋሰስ ከፍተኛ የኾነ የአፈር ክለት ያለበት፣ በሥሩ ደግሞ ጣና ሐይቅ እና የሕዳሴው ግድብን ጨምሮ ሌሎች ውኃማ አካላትን የያዘ ተፋሰስ ነው።

በተፋሰሱ ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ ከ1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ ተሠርቷል። የተፈጥሮ ሃብት ሥራው ደግሞ የአፈር ክለትን በመቀነስ ውኃማ አካላት እና የመስኖ መሠረተ ልማቶች በደለል ሳይሞሉ ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ እና የሰብል፣ እንስሳት እና ፍራፍሬ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ አላማ ያደረገ ነው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብት ሥራ የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ በተወሰኑ ወራት ብቻ ተሠርቶ የሚቆም ሳይኾን ዓመቱን ሙሉ በትኩረት የሚሠራ ነው።

ለዚህ ደግሞ የክልሉን የደን ሽፋን ለማሳደግ በበጋው ወራት የተሠራውን የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራ በክረምት ወራት በአረንጓዴ አሻራ የማጠናከር ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

በዓባይ ተፋሰስ ብቻ ከ5 ሚሊዮን በላይ መሬት በተለያዩ ችግኞች በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተከላ ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።

ከ140 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ እና የተጋጋጠ መሬት በመከለል እንዲያገግም መደረጉንም በማሳያነት አንስተዋል።

እንደ ክልል ደግሞ ላለፉት አምስት ዓመታት ከ5 ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተከላ ተካሂዷል። ከተከላው ጎን ለጎን ደግሞ የተራቆቱ እና የተጋጋጡ መሬቶች እንዲጠበቁ ተደርጓል።

በተሠራው ሥራ የአፈር እና ውኃ እቀባ ሥራው ሲጀምር ከ5 እስከ 7 በመቶ የነበረውን የደን ሽፋን አሁን ላይ ወደ 16 ነጥብ 3 በመቶ ማሳደግ ተችሏል።

የተሠሩ ሥራዎችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ በዋናነት የማኅበረሰቡ ኀላፊነት ቢኾንም በራሳቸው መተዳደሪያ ደንብ የሚሠሩ የተፋሰስ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እንዲቋቋሙ መደረጉንም ነው የገለጹት።

ማኅበራቱ ከተፋሰሱ እንዲጠቀሙ ተደርጎ የተመሠረቱ ናቸው። ከኅብረት ሥራ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ጋር በቅንጅት እንዲሠሩ መደረጉንም ገልጸዋል።

ከማምረትበላይ

BeyondProduction

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *