/ሶዶ፣ ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/
የደን መጨፍጨፍ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በግብርናው ምርትና ምርታማነት እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ አሳድሮ ቆይቷል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት መንግስት ባለፉት አመታት በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢችን በተፈጥሯዊ መልሶ ማልማት(Natural Regeneration) እና ችግኞችን በመትከል (enrichment plantation) አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ የተራቆቱ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ባለፉት 6 ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የአገራችንን የደን ሽፋን ከነበረበት ዝቅተኛ ቁጥር ወደ 23 በመቶ ማድረስ ተችሏል፡፡ በዚህም የለሙ የማህበረሰብ ደኖችን ባለቤት እንዲኖራቸው እየተደረገ ይገኛል፡፡
መንግስት የያዘውን የአረንጓዴ ልማት ኢኮኖሚ መሰረት በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ በአርሶአደሩ ኑሮና የግብርና እንቅስቃሴ ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚከናወኑ ስራዎችን በመደገፍ ሂደት ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ትልቅ ተሞክሮ ያላቸው ስራዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እያከናወነ ይገኛል፡፡
አርሶአደሩ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እራሱ የሚያስተዳድረው፣ የሚንከባከበው፣ የሚጠብቀውና የሚጠቀምበት የአሰራር ዘዴ የሆነውን የተፈጥሮ ደንን መልሶ ማልማት ( Farmer Managed Natural Regeneration(FMNR)) ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል፡፡
FMNR እየተተገበረባቸው ባሉ አካባቢዎች አርሶአደሮች በማህበር በመደራጀት የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማታቸው የአፈር ለምነት እና የሰብል ምርታማነት መጨመር፣ የተሻሻለ የእንስሳት መኖ እና የማገዶ አቅርቦት መጨመር ከማምጣቱም ባለፈ የቤተሰብ ገቢ እና የተሻለ የኑሮ ደረጃ ማምጣት፣ የምንጭ ውሃ መጎልበትና የብዝሃ ህይወት መጨመር ታይቷል፡፡
ይህ ውጤታማ ስራ ከተከናወነባቸው ቦታዎች አንዱ የወላይታ ዞን ሲሆን ድርጅቱ ከማህበረሰቡና ከመንግስት ጋር በመተባበር ከ18 ሺ ሄክታር በላይ ለበርካታ አመታት ተራቁተው የነበሩ ቦታዎችን መልሶ በማልማትና በደን በመሸፈን የአካባቢውን አርሶአደሮች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እና አካባቢ ፕሮጀክቶች ማናጀር ከበደ ረጋሳ የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የደን ሽፋንን ለማሳደግና የግብርናውን ምርታማነትና የማህበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል በአርሶአደር የሚመራና የሚተዳደር የደን መልሶ ማልማት ዘዴን በመጠቀም ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
የአርሶአደር መር አሰራር ተግባራዊ መሆኑ በለሙና በሚለሙ ደኖች ላይ ለማህበራቱ የባለቤትነት ስሜት በመፍጠር ልማቱን እንዲንከባከቡት ማድረግ መቻሉን ማናጀሩ ተናግረዋል፡፡
አርሶአደሩን በማህበር በማደራጀት በየአካባቢው ያሉ የተራቆቱ መሬቶችን በመከለልና በመንከባከብ በተፈጥሯዊ መልሶ ማልማት ዘዴ ማገገም እንዲችሉ በስፋት መሰራቱን ማናጀሩ ገልጸው በዚህ ብቻ የማይመለሱትን ደግሞ በችግኝ ተካላ (enrichment plantation) በማገዝ በአርሶአደሩ ኑሮና ግብርና ምርታማነት ላይ ትልቅ ለውጥ መታየቱን ተናግረዋል፡፡
የተራቆቱ አካባቢዎች ሲከለሉ ለከሰል፣ ለግጦሽና ለማገዶ ይጠቀሙ የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች እንዳይጎዱ አማራጭ የገቢ ምንጭ በመፍጠር መልሶ በለማው ደን እና በየቤታቸው እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የደን ማህበራት የካርቦን ሽያጭ በማድረግ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ነው፡፡
በወላይታ ዞን ደን አካባቢ ጥበቃና ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ መርክነህ ማለደ በበኩላቸው ከደን ልማት አንጻር ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በጋራ እሰሩ መሆኑን ገልፀው የተራቆቱና የተጎዱ መሬቶችን መልሶ በማልማት የአርሶአደሩን ምርታማነት ማሳደግ በመቻሉ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተራቆቱ መሬቶችን መልሶ በማልማት ሂደት አርሶአደር ማሰልጠን፣ ግንዛቤ መፍጠርና የደን ማህበራትን የማደራጀት ስራዎች በመሰራታቸው ደኖች ባለቤት እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡ በዚህም ማህበረሰቡ የባለቤትነት ስሜት በመገንባቱ ልማቱ ውጤታማ ሆኗል፡፡
ወርልድ ቪዝን ከዞኑ ጋር በትብብር በመስራት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማቱ የአካባቢ ስነ-ምህዳር መሻሻሉን እና የግብርና ምርታማነት መጨመሩን ኃላፊው ገልፀው የካርቦን ሽያጭ እና የምንጮች መጎልበት እንዲሁም የኃይል ማመንጫ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ማስቻሉ ዋና ዋና የተገኙ ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ የተገኙ ተሞክሮዎችን በመውሰድ መንግስት ሌሎች የተራቆቱ ቦታዎችን በመለየት በስፋት እያለማ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በዞኑ ሆቢቻ ወረዳ ወይጦ ተራራ ደን ልማትና ግብርና ምርቶች ግብይት ህ/ስ/ማ ሰብሳቢ አርሶአደር መኮንን ጉጆ ከዚህ በፊት ተራራው ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ለከሰል፣ ማገዶና ለልቅ ግጦሽ በመዋሉ በከፍተኛ ደረጃ ለመሬት መራቆት ተዳርጎ እንደነበርና ማህበረሰቡን ለተለያዩ ችግሮች አጋልጦት እንደነበር ገልፀው በደን ልማት ማህበር በመደራጀት ቦታው በመከለሉና እንክብካቤ በመደረጉ አሁን የተፈጥሮ ገፅታው እንደተመለሰ ተናግረዋል፡፡
የዱር እንስሳት ወደ ነባር መኖሪያቸው እየተመለሱ መሆኑን አርሶአደር መኮንን ገልፀው በከሰል ሽያጭ ይተዳደሩ ለነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ሌላ የገቢ አማራጭ በተለይም አትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት መኖ ልማት፣ ንብ ማነብ፣ ፍየልና በግ በማርባት ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡ ለደን መልሶ ልማቱ በቂ ግንዛቤ ስለተፈጠረለትና ጠቀሜታውን በተግባር እየተረዳ በመምጣቱ ልማቱ የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር፣ የአካባቢ ስነ-ምህዳር እንዲጠበቅ፣ የእርሻና መኖሪያ ቤቶች በጎርፍ እንዳይጎዱ ከማድረጉ ባለፈ ማህበራቸው ወደ ካርቦን ሽያጭ በመግባቱ በየአመቱ ተጨማሪ ገቢ እያስገኘላቸው እንደሚገኝ አርሶአደሩ ተናግረዋል፡፡ በዚህም የማህበሩ አባላት ከችግር ተምረው ችግርን በማሸነፍ ጥሩ ገቢ እያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የደን መልሶ ማልማት ስራው ከተራራው ስር ያሉ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች በጎርፍ እንዳይጎዱ ከማድረጉ ባለፈ የተረጋጋና ዘላቂ ውሃና ርጥበት ስለሚሰጣቸው የግብርና ምርትና ምርታማነቱ እያደገ መጥቷል፡፡
ዘጋቢ፡- ተዋበ ጫኔ
ፎቶግራፍ፡- ማቲዎስ ተገኝ