በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ መሬቶችን በማከም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ ነው።
-የግብርና ሚኒስቴር ሚንስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)
(አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2016 ዓ.ም፤ ግብርና ሚኒስቴር)
በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ መሬቶችን በማከም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የጉደር ኖራ ማዘጋጃ ፋብሪካን ጎብኝተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በጉብኝቱ ወቅት፤ በኢትዮጵያ ከሚታረሰው መሬት ውስጥ 43 በመቶ የሚሆነው በአሲዳማነት የተጠቃ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን የአፈር አሲዳማነት በማከም ምርታማነትን ለመጨመር የተለያዩ ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም የኖራ ፋብሪካዎችን አቅም የማሳደግና አዳዲስ ፋብሪካዎችን በተለያዩ ቦታዎች ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በሌላ መልኩም የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ኖራን እንዲያመርቱ መግባባት ላይ መደረሱንም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል የጉደር ኖራ ማዘጋጃን ጨምሮ በአማራ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች በአጠቃላይ ሦስት የኖራ ማዘጋጃ ፋብሪካዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) ግብርና የሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በመሆኑ ዘርፉን ማገዝ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስቴር በአፈር አሲዳማነት የተጠቁ መሬቶችን ለማከም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ፤ በክልሉ ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው ብለዋል።
ይህን በኖራ እና በሌሎችም ዘዴዎች በማከም ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የጉደር ኖራ ማዘጋጃ ፋብሪካ በቀን ከ1ሺህ እስከ 4 ሺህ ኩንታል ኖራ በማምረት ላይ እንደሚገኝ በጉብኝቱ ተጠቅሷል።
በጉብኝቱ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹን ጨምሮ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የዘገባ ምንጫችን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ነው።