FDRE Ministry of Agriculture

በትንሽ ቦታ ብዙ ማምረት!

(ሐዋሳ፣ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “ምግቤን ከጓሮዬ” በሚል መርህ የከተማ ግብርና ልማት ስራ መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም በከተማ የሚኖር አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍሎች ማለት በሚቻል ደረጃ ይብዛም ይነስም ባለው የክፍት ቦታ ላይ የተለያዩ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ የእንስሳት ርባታ፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እንዲሁም የንብ ማነብ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በዚህም ተግባር በከተማ ውስጥ የምግብ ፍጆታ ዋጋን የማረጋጋት፣ የስራ ዕድል መፍጠር እንዲሁም ሌሎች ዘርፈ-ብዙ ጥቅሞች እየተገኙበት ነው፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የከተማ ግብርና መሪ ስራ አስፈፃሚ አስተባባሪነት ከሲዳማ ክልል፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሁም ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ23 ከተሞች ለተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች ልምድ ልውውጥን ታሳቢ ያደረገ የጉብኝት መርሃ-ግብር በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በዚህም በከተማ ግብርና ልማት ስራ በእንስሳት ዘርፍ (የከብት ማድለብ ስራዎች፣ የአንድ ቀን ጫጩት እርባታ፣ የወተት ላም እርባታ እንዲሁም የንብ ማነብ ስራዎች) በተጨማሪም በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በቅመማቅመም ልማት የተሰሩ ምርጥ ተሞክሮዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡
በሚኒስቴሩ የከተማ ግብርና መሪ ስራ አስፈፃሚ ስለሺ በቀለ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ ባለፉት ሶስት ዓመታትም ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ፣ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት እንዲሁም ከሌሎች ሃገራት ልምድ በመውሰድ የከተማ ግብርናን ለማስፋፋትና ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የከተማ ግብርና ልማት ስራ በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ማምረት እንደሚቻል የታየበት መሆኑን መሪ ስራ አስፈፃሚው አብራርተዋል፡፡
በከተሞች አካባቢ የከተማ ግብርና ልማት ስራን በተቀናጀ መንገድ ማስፋፋት እና ማሳደግ እንደሚገባም አያይዘው ተናግረዋል፡፡
ጉብኝት ከተደረገባቸው መካከልም የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የወሳኝ ኩነት ምዝገባና አስተዳደር ኤጀንሲ አንዱ ሲሆን በኤጀንሲው ቅጥር ጊቢ ውስጥ የተለያዩ የከተማ ግብርና ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ታመነ ተሰማ፣ ኤጀንሲው በመንግስት ከተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ጎን ለጎን የተቀናጀ የከተማ ግብርና ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡
በከተማ ግብርና ስራው ለምግብ የሚሆኑ ምርቶችን ከማምረት ባሻገር ለሰራተኞች ምቹ የሆነ የስራ ቦታ እንዲፈጠርላቸው እንዳስቻለ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የሚመረቱ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬዎች፣ የዶሮ ርባታ፣ የንብ ማነብ ስራ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ምርቶችን በአካባቢው ለሚገኙ አቅመ ደካማ የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ በተጨማሪም ለተቋሙ ሰራተኞች እና ለሌሎች ሴክተር መ/ቤት ሰራተኞች የግብርና ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ እያቀረቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በጉብኝቱ የተሳተፉ የዘርፉ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ማምረት የተቻለበትን ተሞክሮ ማየት እንደቻሉና በአካባቢያቸው ተግባራዊ ለማድረግ ልምድ መቅሰም እንደቻሉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው
ፎቶግራፍ፡- ያሬድ አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *