በቀጣዮቹ 10 ቀናት በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ የዝናብ ስርጭት ይኖራል- ኢንስቲትዩቱ
(አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣ 2016 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
በሚቀጥሉት አሥር ቀናት በምዕራብ አጋማሽ የሀገሪቱ ክፍሎች የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በዚሁ መሰረት በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቡኖ በደሌ፣ ጅማ፣ ኢሉአባቦር፣ ማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር፣ አዊ ዞን፣ አሶሳ፣ ካማሺ፣ መተከል እና የማኦ ኮሞ ልዩ ዞን የተሻለ የዝናብ መጠን እንደሚኖራቸው የኢንስቲትዩቱ መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ቤንች ሸኮ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካ፣ ኮንታ እና ምዕራብ ኦሞ፣ ባስኬቶ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ወላይታ እና ጌዲዮ፣ ሀላባ፣ ሃዲያ፣ ጠምባሮ እና የየም ልዩ ዞን፣ ማዣንግ፣ አኝዋክ፣ የኢታንግ ልዩ ዞን እና ንዌር ዞኖች የተሻለ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደሚኖራቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ባሌ፣ አርሲ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ ዞኖች፣ አዲስ አበባ፣ ድሬ ዳዋ እና ሐረር ከተሞች፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር፣ የትግራይ ክልል ምዕራብ እና ሰሜን ምዕራብ ዞኖች፣ ኮንሶ፣ አማሮ፣ አሌ፣ ቡርጂ፣ ደራሼ፣ ጉራጌ እና ስልጤ ዞኖች ቀላል መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል፡፡
የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት በሰሜን ምሥራቅ እና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከ 35 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆንም ነው የተመላከተው ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቦታል።