FDRE Ministry of Agriculture

ለግብርና ኢንቨስትመንት ውጤታማነት ክልል-አቀፍ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ሚና

የግብርና ኢንቨስትመንት ለብሔራዊ ኢኮኖሚ እድገት፣ ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለምግብ አቅርቦት፣ ለድህነት ቅነሳ፣ ለጥሬ ዕቃ አቅርቦት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ያለው ሚና የሚናቅ አይደለም፡፡ መንግስት እንደ ሀገር  2.2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በግብርና ላይ ለተሰማሩ 6000 ባለሀብቶች እንዳስተላለፈ መረጃው ያመለክታል፡፡ በ10 ዓመቱ መሪ እቅድ መሰረት እ.አ.አ እስከ  2030 መጨረሻ ድረስ 4.2 ሚሊዮን ሄክታር  መሬት ለማስተላለፍ ዕቅድ ተይዟል፡፡ እስከ አሁን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ብቻ 430 ባለሀብቶች በግብርና ላይ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡

/አዲስ አበባ፣ ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር/

ግብርና ሚኒስቴር  የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን በማህበረሰብ ውስጥ የማረጋገጥ፣ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን  በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት፣ ኤክስፖርትን በማበረታታት  የውጪ ምንዛሪ ግኝትን የማሳደግ እና የስራ ዕድል የመፍጠር  ግቦችን አስቀምጦ በትኩረት እየሰራ ሲሆን እነዚህን ግቦች ለማሳካት የግብርና  ኢንቨስትመንት ጉልህ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን  በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ያለውን የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማጠናከር የተካሄደው ክልል-አቀፍ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ለአብነት ይጠቀሳል፡፡

የምክክር መድረኩ ግብርና ሚኒስቴርን፣ የደቡብብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን፣ በክልሉ የግብርና ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ውጤታማ ስራዎች የተሰሩበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ በክልሉ በሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ተሰማርተው የወሰዱትን መሬት በአግባቡ አልምተው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ መልካም ተሞክሮ ያላቸው ባለሀብቶች ልምዳቸውን ለሌሎች አካፍለዋል፤ በመስክ ጉብኝትም በተጨባጭ ልምድ እንዲቀስሙ ተደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል፣ መድረኩ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት  የነበረባቸውን ክፍተቶችና ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለይተው እንዲያዩ አስችሏቸዋል፡፡ መሬት ወስደው በሚፈለገው ልክ አለማልማት፣ ለወሰዱት ዓለማ አለማዋል፣ ብቃት ያለው ባለሙያ አለመቅጠር፣ ካመረቱ በኋላ በክልሉ እሰት አለመፍጠር፣ ህገወጥ የቡና ንግድና በሌላ አካባቢ ብራንድ መሸጥ እንዲሁም ከመንገድ፣ ከመልካም አስተዳደር  እና ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር የተያያዙ ችግሮች ከተነሱት ነጥቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ችግሮችን ነቅሶ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ባለድርሻ አካላቱ የመፍትሄ አካል ሆነው  በጋራ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የድርሻቸውን  በአግባብ ለመወጣት ቃል የገቡበት መድረክ ነው፡፡ በተጨማሪም ክልሉ ባለው ምቹ ሁኔታና ፀጋ ልክ በእንስሳት ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ስላልተሰራ በቀጣይ ዘርፉን ለማዘመንና በትኩረት ለመምራት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

እንዲሁም መድረኩ በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል መተማመንን ከመፍጠሩም ባሻገር ቅንጅታዊ አሰራርን ያጎለበተ ነበር፡፡

በመሆኑም የግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ክልል-አቀፍ የግብርና ኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በሌሎች ክልሎችም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡