FDRE Ministry of Agriculture

የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤታማነት በምስራቅ ሀረርጌ ዞን

ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል፡፡ የማህበረሰብ ስራ ሰርተው ከሚያገኙት ክፍያ በመቆጠብ እና የተመቻቸላቸውን ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ብር ተበድረው የተለያዩ ስራዎችን በመስራት  ኑሯቸውን የቀየሩ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች በርካታ ናቸው፡፡ እንዲሁም የተጎዱ አካባቢዎች አገግመው እንዲለሙ በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ፕሮግራሙ ጉልህ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ውጤት ካመጣባቸው ዞኖች መካከል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን አንዱ ነው፡፡

በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ግብርና ጽ/ቤት የምግብ ዋስትና ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዘከሪያ ሻም ፕሮግራሙ በዞኑ ውስጥ በተጠቃሚዎች ኑሮ እና በአካባቢው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ዘከሪያ ገለፃ በሚከፈላቸው ክፍያ ተጠቃሚዎች የምግብ ክፍተትን በመሙላት በህይወት እንዲኖሩ ማድረግ ተችሏል፡፡ ተጠቃሚዎቹ  በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ዘዴ በኩል ብድር አግኝተው የተለያዩ ስራዎችን ሰርተው ሀብት ማፍራት ችለዋል፡፡ ዛሬ  አበዳሪዎች ያለምንም ጥርጣሬ ያበድሯቸዋል፤ እነሱም በራሳቸው በመተማመን ለሚፈልጉት ስራ ይበደራሉ፡፡

ዘንድሮ ከቶኩማ እሬ ቀበሌ ብቻ ለ73  ተጠቃሚዎች ብድር ተሰጥቷል ያሉት አቶ ዘከሪያ፣ በተበደሩት ብር ዶሮዎችና ፈየሎችን ገዝተው በማርባትና አደልበው በመሸጥ ገቢ እንደሚያገኙና የስርዓተ-ምግብ ችግሮቻቸውንም እየፈቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ከሳር ቤት ወደ ቆረቆሮ፣ ከጠባብ ቤት ወደ ሰፊ መኖሪያ ቤት መሸጋገራቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አቶ ዘከሪያ እንደገለፁት በተፋሰስ ልማት አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ በፕሮግራሙ አገግመው ከለሙ አካባቢዎች መካከል በጉረዋ ወረዳ ቶኩማ እሬ ቀበሌ ውስጥ የሚገኘው የቦረማ ተፋሰስ አንዱ ነው፡፡ ይህ ተፋሰስ በፊት ምንም ዛፍ ያልነበረው፣ አፈሩ ታጥቦ ገላጣ በመሆን እጅግ የተጎዳ ነበር፡፡ ትኩረት ተሰጥቶ በቁርጠኝነት በተለያዩ ስትራክቸሮች ስለተሰራ ዛሬ በዛፍ ተሸፍኖ አረንጓዴ ሆኗል፡፡ ዝናብ በዘነበ ቁጥር ከጋራ ላይ ወርዶ ጉዳት የሚያደርሰው ጎርፍና የአፈር መሸርሸር ቆሟል፡፡ የዝናብ ሁኔታ ተሸሽለዋል፤  ዘግይቶ ይጀምርና ቀድሞ ይወጣ የነበረው ዝናብ እየተስተካከለ መጥቷል፡፡

አቶ ዘከሪያ የደረቁ ምንጮች ፈልቀው፣ የነበሩ ጎልበተው ለመስኖ እየዋሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣  በዚህ ምክንያት የግብርና ምርትና ምርታመነትም እየጨመረ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመሬት ጥበትና በዝናብ እጥረት ነው እንጂ ለከፋ ችግር የተጋለጠው የሀረርጌ አርሶአደር በስራ አይወቀስም ያሉት አስተባባሪው፣ በተጨማሪነት መንግስት ድህነትን ለመቀነስ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከላይ እስከታች በተሰጠው ስልጠና ህዝቡ ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለማሸጋገር በቂ ግንዛቤ ማግኘቱን ገልፀዋል፡፡ ተጠቃሚዎቹ የተፈጠረላቸውን ምቹ ሁኔታ በአግባቡ ተጠቅመው ከድህነት ለመውጣት ባደረጉት ጥረት  ዘንድሮ 228 ሺህ ተጠቃሚዎችን ለማስመረቅ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

አርሶአደር ቶፊቅ አብዲ የተኩማ እሬ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የመህበረሰብ ስራ ሰርተው ከፕሮግራሙ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ በተመቻቸላቸው የብድር ሁኔታ ከሲንቄ ባንከ 12 ሺህ ብር በመበደር 2 ፍየሎችን በ9200 ብር ገዝተው ማድለብ ጀመሩ፡፡ አደልበውም በ13300 ብር በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት ጀመሩ፡፡ ዛሬ  የቤተሰባቸውን ኑሮ አሻሽለው ልጆቻቸውን እያስተማሩ  ያሉት አርሶአደር ቶፊቅ፣ የማድለብ ስራውን አጠናክረው እንደሚጥሉም ተናግረዋል፡፡

የቶኩማ እሬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ፋጡማ አብዱረዛቀ እና አርሶአደር አቡሌ መሐመድስራጅ ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ ኑሯቸውን የቀየሩ ናቸው፡፡ ፍየሎችን በማድለብ ውጤታማ ሆነዋል፤ ባነጋገርናቸው ጊዜ አራት አራት ሙክቶችን ለሽያጭ አድርሰዋል፡፡ ከፕሮግራሙ በራሳቸው ፍቃድ ለመመረቅ ዝግጁ መሆናቸውንና የማድለብ ስራውንም አጠናክረው ለመቀጠል እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሸምሱዲን ዩሱፍ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *