FDRE Ministry of Agriculture

የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት የዘርፉን ምርታማነት ለማሳደግ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

(ቢሾፍቱ፣ ህዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)

የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት የተሰጠውን ተልዕኮ ለመወጣት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡ ተቋሙ የእንስሳት በሽታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል የምርምርና ምርመራ ስራዎችን በማከናወን ሀገራችን በዘርፉ በአለምአቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንድትሆን የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

በቆላ ዝንብና በገንዲ በሽታ በተጠቁ የሀገራችን አካባቢዎች የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የማጥፋት ስራዎችንም በተጠናከረ መልኩ በማካሄድ የእንስሳትን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እና በእንስሳት ጤና ላይ የስልጠናና የማማከር ስራዎችን በማከናወን በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትን አቅም ማጎልበት ላይ አላማውን አድርጎ እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት የተሰጡትን ኃላፊነቶች ለመወጣት እንዲያስችለው የተለያዩ ሶስት ስትራቴጂክ ሰነዶችን፤ የእንስሳት ጤና ምርምር የአምስት አመት ስትራቴጂ፣ የቆላ ዝንብና ገንዲ በሽታ የአስር አመት ሂደታዊ መቆጣጠሪያና ማጥፊያ ስትራቴጂ እንዲሁም የወጪ መጋራት መመሪያ አዘጋጅቷል፡፡

እነዚህንም ሰነዶች ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ሃሳብና አስተያየቶችን በማሰባሰብ ሰነዶቹን ለማደበር የሚያስችል ለሁለት ቀናት የሚቆይ አውደ-ጥናት በዛሬው ዕለት የተጀመረ ሲሆን በዚህም ሰነዶቹን ለማዳበር የሚረዱ ግብዓቶች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ሩፋኤል (ዶ/ር) የእንስሳት በሽታን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስተማማኝ የሆነ የእንስሳት ጤና የምርምር ስራዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የተዘጋጁት የእንስሳት ጤና ምርምር ስትራቴጂዎችና ሌሎች ሰነዶች የተቋሙን አቅም በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና ዓሳ ሃብት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አለማየሁ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት አመታት በርካታ ፈተናዎችን አልፎ አሁን ላይ ትልቅ ተቋም መሆን ችሏል ብለዋል፡፡

አማካሪው አክለውም የእንስሳት ጤና ግብዓት አቅርቦት ላይ በቅንጅት በመስራት የዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ሀገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ማሳደግ እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል፡፡

አማካሪው አያይዘውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋ ፕሮግራም ለእንስሳትና ዓሳ ሃብት ዘርፍ ትልቅ መነቃቃትን እንደፈጠረ ጠቁመዋል፡፡

በአውደ-ጥናቱ ላይም የተዘጋጁት ሶስት ስትራቴጂክ ሰነዶች የቀረቡ ሲሆን ተሳታፊዎችም በቀረቡት ስትራቴጂክ ሰነዶች ላይ ገንቢ ሃሳቦች በመስጠት ተወያይተዋል፡፡

በዚህም አውደ-ጥናት ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከክልል ግብርናና እንስሳት ሃብት ቢሮ፣ ከህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የእንስሳት ጤና ላቦራቶሪዎች፣ ከምርምር ተቋማት፣ ከህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ሰለሞን ደምሰው

ፎቶግራፍ፡- ጌታቸው ምትኩ