(አዲስ አበባ፣ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር)
የሌማት ትሩፋት ለግብርና ኢንቨስትመንትና ለሀገራዊ የስርዓተ ምግብ መሻሻል ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተገልጿል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በደብረ ብርሃን ከተማ በሌማት ትሩፋት የተሰማራ የውጭ ባለሃብት የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ባቀድነው መሠረት በውጤታማነት እየተተገበረ ነው ብለዋል። የተመጣጠነ የምግብ ዋስትና ስርዓትን ለማረጋገጥ በሁሉም መስክ የተጀመሩ ሥራዎች የሚበረታቱ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የደብረ-ሆላንድ የዶሮና እንቁላል ምርት ማዕከልም ሀገራዊ ውጥንን ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ማዕከሉ ከ90 ሺህ በላይ እንቁላል በየቀኑ እያመረተ ለገበያ በቂ ምርት እንዲቀርብ እና በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚ እንዲደርስ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ፥ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭ ከሁለት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መተግበር ከጀመረ ወዲህ ውጤታማ ሆኗል ብለዋል።
ዘንድሮ በዓመት 110 ሚሊዮን ጫጩት ማስፈልፈል የሚችል ፕሮጀክት ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት 150 ሚሊዮን የአንድ ቀን ጫጩት ለማሰራጨት መታቀዱን ገልጸው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ20 ሚሊዮን በላይ ጫጩት መሰራጨቱን ጠቅሰዋል። የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የዶሮ ስጋ እና የእንቁላል ምርትን በመጨመር የምግብ ስርዓታችንን እያሻሻለ ነው ብለዋል።
በእንስሳትና ወተት፣ በአሳ፣ በንብ ማነብ ሥራም ከፍተኛ መነቃቃት መታየቱን ጠቅሰዋል። ዘርፉ ለግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ እና ከፍተኛ የገበያ ፍላጎት በመኖሩ በርካታ ባለሀብቶች በመሰማራት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የደብረ ሆላንድ የዶሮና እንቁላል ምርት ማዕከልም በስጋ ዶሮ እና በእንቁላል ምርት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ለማህበረሰቡ የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በክልሉ በስምንት የሪጂዮፖሊታን ከተሞች የሌማት ትሩፋት ማዕከላትን በማደራጀት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
በገጠር ወረዳዎችም በርካታ ወጣቶች ውጤት እያመጡበት ነው ያሉት ኃላፊው፤ በዘርፉ በኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችም መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።